ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ

ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ
~•~
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም መነሻም መሰረቱም ህብረብሔራዊ ወይም በማንነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራል ሲስተም ወይም ስርዓት ነው።
በህገ መንግስቱ መሰረት ማንኛውም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት ያለ ገደብ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መብት መሰረትም በማንነት ላይ የተዋቀረ ከወረዳ እስከ ክልል የመቋቋም መብት እንዳላቸው ነው።
የሐረሪ ሕዝብ የረዥም ዘመናት ታሪክ ባህልና ቋንቋው እንዲሁም በነፃ መንግስት አስተዳደሩ መናገሻና እምብርት የዳበረው ባህላዊ እውቀቱና ጥበብ ያንፀባረቀበት ጀጎል ከማንነት መገለጫዎቹ መካከል ህያው ቅርሶቻቸው ያኖረ ድንቅ ህዝብ ነው፡፡ የሐረሪ ህዝብ ከሰፊ ግዛት፣ ከጠንካራ መንግስትና ሉአላዊነት ከመጀመሪያው አሚር ሐቦብ ከ969-1887 እ.ኤ.አ እስከ መጨረሻው መሪ አሚር አብዱላሂ ሰባ ሁለት አሚሮች በተፈራረቁበት ሉአላዊ መንግስት ራሱን ሲያስተዳድር የቆየ ህዝብ ነበር፡፡
የሐረሪ ህዝብ በዚህ ዘመን ያገኘው ክልላዊነትና ግዛት ከነበረው ጠንካራ ታሪካዊ መሰረት የሚያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም። ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል እኩል ናቸው። የሐረሪ ብሔር በቁጥር አናሳ በመሆኑ ሌላውን ብሔር በንፅፅር በማቅረብ ክልልነት እንደማይገባው የሚወቅሱ ፅንፈኞች በአደባባይ እያራገቡ ሲቀባበሉ ይታያሉ። የሐረሪ ማንነትና ስሌት በሌላው እየተለካ የሚነቀፍበት አግባብ ከታሪክ ማንነት በቅጡ ያለመረዳት ብሎም ርካሽ የፖለቲካ ድለላና ችርቻሮ የፈጠረው አባዜ መሆኑን ማንም ሊረዳው ይገባል።
እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጅምር ፌደራል ስርዓት ግንባታ ላይ ያሉ ቀርቶ በአለም ላይ የተሳካ የፌደራል ስርዓት መስረተዋል የሚባሉ ሀገራት እንከን እና ችግር አልባ የፌደራል ስራዓት ምስረታ ጉዞ በታሪክ ሂደት ሆኖላቸው አያውቅም። በአሁኑ ጊዜ ጠንካራ የሆኑ ፌድራል ሀገራት በፌደራል ስርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮች በሂደት እየቀረፉ ጠንካራ ደረጃ ላይ ሁሉም የደረሱ ናቸው።
የኢትዮጵያ የፌድራል ስራዓት አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ በሂደት የታዩትን ችግሮች በማጥናት አስፈላጊውን ferderal reform በማድረግ የፌደራል ስርዓት ማጠናከር ይቻላል። ሆኖም ግን ፅንፈኛ አሃዳዊ አመለካከት ያለቸው አካላት በተቃራኒው የማፍረስ የፖለቲካ ፍላጎታቸው ሲያንፀባርቁ ይታያሉ።
በጣም የሚያሳዝናው ግን ከእውቀት የፀዱ አንዳንድ አዋቂ፣ መሁርና ፖለቲከኛ ነን ከሚለሉ ጀምሮ እስከ ተራ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ፌደራልዝም ለማጥላላት ዘመቻ የሚጀምሩት የሐረሪ ክልል በማጣፈጫነት ካላነሱ ስካራቸው የማይበርድላቸው መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ የፌድራል ስርዓት በህገ መንግስቱ መሰረት የሐረሪ ክልልነት አለአግባብ ሰቶ ሌላው የከለከለበት አግባብ እንደሌለ ይታወቃል።
በማንነት መሰረት ያረፈ አስተዳደር የተጀመረው ካለፉት ሥርአቶች በተለየ ሁኔታ የህዝቦች ነፃነት፣ የብሄሮችና የሃይማኖቶች እኩልነት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተረጋገጠባት አዲሲቷን ኢትዮጲያ ለመመስረት መሰረት የተጣለው ሰኔ 24/1983 ዓ.ም. ብሔራዊ ኮንፈረንስ በማድረግ በቻርተር የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም በተደረገው ነበር።
ቻርተሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የእኩልነት መብቶች እንዲሁም ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ማንነታቸውን፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን የመግለጽ፣ በቋንቋው የመጠቀምና የማሳደግ መብት ያረጋገጠ እንደነበረ እሙን ነው ።
የብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር ዝርዝር አፈፃፀሙን በተመለከተም የሽግግሩ መንግስት ምክር ቤት ባወጣቸው አዋጅ ቁጥር 7/84 በይፋ የተገለፀበት ነበር። በተግባርም 14 ክልሎችና በርካታ ወረዳዎች ተቋቅመው ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እንዲበቁ አስችሏል። በአዋጁ ወደ 65 የሚሆኑ ብሔር ቋንቋ ማህበረሰብ እውቅና የሰጠ ቢሆንም በዋናናት በ 14 ራሳቸውን የቻሉ ነፃ ክልላት አዋቅሯል። በወቅቱ በማንነት ላይ መሰረት ያደረገ ክልል ሆኖ ለማስተዳደርም የተሟላ መንግስታዊ መዋቅር መዘርጋትና ተፈላጊው የሰው ሃይል ማግኘት ትልቅ ፈተና እንደነበረም ይታወቃል።
በክልል ደረጃ የተዋቀሩት ውስጥ ሲዳማም እና ጉራጌም ራሳቸው የቻሉ ክልሎች እንደነበሩ ይታውቃል። የሐረሪ ክልልም በክልል 13 ስም በአዋጁ ሐረሪዎች ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድር ያጎናፀፈ እንደነበር ይታወቃል።
የሲዳማም ሆነ የጉራጌ ህዝብ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች የነበሩ ቢሆንም በ1987ቱ ህገ መንግስት አምስት ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች( ክልል 7፣ 8፣ 9፣ 10 እና 11) ፍላጎት ወደ አንድ ክልል የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲዋቀር ተደርጓል።
አንዳንዱ በተሳሳተ አረዳድ፣ በመታወር፣ በመደንቆር ወይም በመጥፎ ፍላጎት ለሐረሪ ክልልነት ተሰጥቶት ሌሎች እንደተከለከሉ ያንፀባርቃሉ። አጓጉል ተቆርቋሪዎችን ይሆናሉ። ዋናው አላማ አንዳንዱ ግን የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማራመድ በክልሉ መብት ላይ ጫና ለመፍጠር እየታተሩ ይገኛሉ።
አንደንዱም የፌድራል ስርዓቱን ለማጥላላትና ለማፍረስ የሚጠቀሙት ስልት ነው። ማንኛውም ብሔር በማንነቱ የማስተደደር ጥያቄ በህጉ አግባብ መጠየቅ በህገ መንግስቱም የተከለከለ የለም። ማንኛውም ብሔር ጥያቄውን ማቅረብ ባልተከለከለበት ሐረሪን ክልል ማንሳቱ ለምን እንዳስፈለገ በጣም የሚገርም ነው።
አዋቂ ነን ባዮች የሐረሪን ክልልነት በእውርነትና በድንቁርና የሚተቹት መሰረት በሌለው ጉዳይና የራሳቸው ርካሽ ፖለቲካ ማራመጃና ማጣፈጫ እኩይ ምኞታቸው የመነጨ ነው። በአንድ ብሔር ማንነት ላይ ያላቸው ንቀት በግልፅ የሚያንፀባርቁ ተግባራቶች ናቸው። ሌላው ክልል የመሆንም ሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሐረሪ ክልልነት ማንሳትም ሳያስፈልግ በህገ መንግስት የማቅረብ ጥያቄ የሚከለክልም የለም።
አዋቂና ሙህር ነን ባዮች ለንፅፅር የሚያቀርቧቸውና የሚመለከታቸው ብሔሮች አንዴም እከሌ ክልል ስለሆነ እኛም ልንሆን ይገባል ብለው የጠየቁም የሉም። በራሱ ማንነት ማስተደደር የፈለገ ብሔር ግን ያለ ንፅፅር በራሱ እያቀረበ ይገኛል።
በሐረሪ ክልል ላይ ያለው ልክፍቱ ፖለቲከኛ አዋቂና ሙህር ነን ባዮች ለግል ጥቅማቸው የወቅቱ የፖለቲካ ድራማ ለመጫወት ሲሉ የሐረሪ የክልልነት ማንሳት እውርናና ድንቁርና ወጤት ነው ከማለት ሌላ ምን ሊባል ይችላን?
አንዳንድ ፅንፈኛ ለማጅ የፖለቲካ ነጋዴ ቡድኖች ከሌላ ክልል ተቆርሶ አለአግባብ ለክልሉ እንደተሰጠ አስመስለው ቅዥታቸውን በሌላው ላይ በግድ ለመጫን የሚያራግቡ አሉ። በክልሉ አናሳ ሆነው እንዴት ያስተዳደራሉ የሚሉ ክፉ ምቀኝነት የተጠናወታቸውም ቡዱኖች
የራሳቸውን ፍላጎት ያለገደብ ያራምዳሉ። የሀረሪ ነፃ አስተዳደር ግዛት ለበርካታ ዘመናት አሁን ክልሉ ከተካለለው ወስን በመቶ እጥፍ በላይ እንደነበረ የአለም ህዝብ የሚመሰክረው ታሪካዊ ሃቅ ነው።
ለዚህ ነው ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ያልኩት አዋቂና ሞሁር ነን ብሎም ፖለቲከኞች ነን ባዮች በህዝብ ስም በመነገድ ለግል ጥቅማቸው የወቅቱ የፖለቲካ ድራማ ለመጫወት ሲሉ የሀረሪ የክልልነትና ማንነት በሚፃረር መልኩ ማንሳት የእወቀት ማነስ ውጤት መገለጫ ነው። እንዲሁም መሰል አመለካከቶችን መሰንዘርና ማራመድ በሀረሪ ማንነት ላይ የተቃጣ ሴራና ደባ ጭምር ነው።
በመጨረሻም የሐረሪ ህዝብ በሁሉም ነገር ቀደምት እንደነበሩ የታሪክ መዛግብቶችን አገላብጥ ። እውነታውን ተረዳ የሐረሪ ህዝብ እንደ ዜጋ ካበረከተው አስተዋፅኦ አንፃር እንኳን ህገመንግስታዊ መብቱን ለመንፈግ መታተር ይቅርና የበለጠ ምስጋና የሚገባው ህዝብ ነበር።
መሆን ያለበት ሳይሆን ቀርቶ መሆን የሌለበትን ለማድረግ የምትፍጨረጨሩ አካለት ሆይ እያንዳንዳችሁ አስራ ስምንት አመት ሞልቶዋችዋል እራሳችሁን ቻሉ የሐረሪን ክልል እና ህዝብን ለቀቅ የራሳችሁን ህገመንግስታዊ የመብት ትያቄያቹን ጠበቅ አድርጉ በማለት አበቃለው ።
ቸር እንሰንብት !