ረመዷን 17 ወሳኝ ዕለት ፈፅሞ ከኡመቱ ቀልብ አትጠፋም!
ታላቁ የበድር ዘመቻ
–
ይህ ረመዳን ለ1441ኛ ጊዜ ሲፆም እኛንም የዚሁ ዘመን ትውልድ አድርጎን የመፆም እድሉን አጎናፀፈን፤ አልሃምዱሊላህ፡፡ ይህ በሒጅራ አቆጣጠር በ2ተኛው ዓመት ፆም ግዴታ የተደረገበት የረመዳን ወር ታላቅ ወር ነው፡፡ በኢስላም ታላላቅና ወሳኝ ለውጦች የተከናወኑበት ወር ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያውና ዋናው፤ በጨረቃ አቆጣጠር ልክ የዛሬ 1440 አመት፤ ልክ በዛሬዋ በረመዳን 17 ዕለት በኢስላም ታሪክ ውስጥ ታላቅ ለውጥ ያመጣ ክስተት ተፈፅሞ ነበር፡፡ ይህን ክስተት በዛሬው ዕለት ሳላስታውስ ማለፉ ስለከበደኝ፤ ምንም እንኳ ታሪኩ ሰፊ ቢሆንም በጣም አሳጥሬም ቢሆን ጥቂት ለመጫር ወሰንኩኝ፡፡
እንደምታውቁት ረሱል صلى الله عليه وسلم በመልዕክተኝነት ከአላህ /ሱ.ወ/ ዘንድ ተልከው መካ ላይ ወደ ኢስላም ጥሪ ማድረግ ከጀመሩ ከጥቂት አመታት
በኋላ ጥሪውን በተቀበሉት ተከታዮቻቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይና መከራ ከመካ ጣዖት አምላኪያን በኩል ተፈፅሞባቸው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ሙስሊሞቹ ቤት ንብረቶቻቸውን ጥለው፤ የአላህን /ሱ.ወ/ ትእዛዝ በማክበር፤ ከትውልድ ሀገራቸው መካ ተነስተው፤ ረሱል . …صلى الله عليه وسلم
‹‹ያጣችሁትን ሁሉ አላህ ይክሳቹሃል››… ወዳሏቸው ሀገር ወደ መዲና ተሰደዱ፡፡ ያንን ሐሩር ቃጠሎን፣ ጥማትን፣ ረሃብንና ድካምን ተቋቁመው ከ450 ኪ.ሜ. በላይ አቋርጠው መዲና ደረሱ፡፡
ከዚያም ከአንድ አመት በኋላ እነዚያ እርኩስ ጣዖት አምላኪያን፤ ሙስሊሞቹ ሲሰደዱ በመካ የተዉትን ንብረቶች በመቆጣጠርና በመዝረፍ የንግድ ዕቃ ሊገዙበት ወደ ሻም ((ወደ ሶሪያ እና በዙሪያዋ ወዳሉ አካባቢዎች)) ካመሩ በኋላ ብዙ ንብረቶችን እና ሸቀጦችን በመሸመት በበርካታ ግመሎች አስጭነውና ገዝተው ወደ መካ ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ይህ ዜና መዲና ውስጥ ወደ ረሱል صلى الله عليه وسلم ደረሰ፡፡ በወቅቱ መዲና
በረሱል صلى الله عليه وسلم እና በሶሐቦቻቸው፤ እንዲሁም ጠላቶቻቸውን ለመፋለም ክንዶቻቸው በጠነከሩ፤ ኃይላቸው በጨመረና፤ መንፈሶቻቸው
በስነልቦና ዝግጁ በሆኑ በሙሀጂሮችና በአንሳሮች፤ ፀጋ መዲና ተሞልታ ነበር፡፡
ይህ እንግዲህ በሂጅራ ሁለተኛ አመት፤ ልክ በዛሬዋ ዕለት፤ በረመዳን 17 ሲሆን፤ በጨረቃ አቆጣጠር ልክ የዛሬ 1440 አመት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ረሱል صلى الله عليه وسلم በጠንካራ መንፈስና በአላህ ላይ በመመካት ጠላትን ለመፋለም ዝግጁ የሆነውን፤ ብዛቱ 313 ገደማ የሚደርሰውን
ጀግናውን የሶሐቦች ሠራዊትን አስከትለው ባንዲራዎችን በዙሪያቸው ከፍ አድርገው እያውለበለቡ አቀኑ፡፡
ሙስሊሞች ለፍልሚያ የመንቀሳቀሳቸው ዜና፤… በዘረፉት የሙስሊሞች ሀብት ሸቀጥ ሸምተው ወደ መካ እየተመለሱ ለሚገኙት ለጣዖታውያኑ የንግድ ጭፍራ ደረሰ፡፡ የነጋዴዎቹን ጭፍራ የሚመራው በወቅቱ የኩፍር ቁንጮ የነበረው ‹‹አቡ-ሱፊያን ኢብኑ ሐርብ›› ነበር፡፡ አቡ ሱፊያን የሚመራው የንግድ ጭፍራ ሸቀጡን ሸክፎ ከሻም ወደ መካ ጉዞ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህ ጭፍራ ከነብዩ صلى الله عليه وسلم ሰራዊት
ሊከላከለው የሚችል በቂ የሆነ ጥበቃ ስላልነበረው፤ የድረሱልኝ ጥሪን እንዲያሰማ ‹‹ደምደም›› የተባለን ሰው ‹‹አቡ-ሱፊያን›› መካ ወደሚገኙት ወገኖቹ ላከ፡፡ ከዚያም ‹‹ደምደም›› መካ ደርሶ ጩኸቱን እና የድርሱልን ጥሪውን አቀለጠው፡፡ በዚህን ጊዜ የመካ ጣዖት አምላኪያን በአፋጣኝ ጦር ሰራዊታቸውን፤ ኃይላቸውንና መሳሪያቸውን አሰባስበው የንግዱን ቡድን ለማዳንና ረሱልን صلى الله عليه وسلم ለመዋጋት
ተንቀሳቀሱ፡፡
በዚህን ወቅት ‹‹አቡ-ሱፍያን›› ከሙስሊሞቹ ሠራዊት ለማምለጥ በማሰብ የተለመደውን የጉዞ መስመር ቀይሮ ነበር፡፡ በተለምዶው ከሻም ወደ መካ ነጋዴዎች የሚጓዙበትን የመንገድ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ባህር በኩል በመቅረብ ጭፍራውን አስከትሎ ወደ መካ ገሰገሰ፡፡
ሙስሊሞቹ ደግሞ የመካ ጣዖት አምላኪያን ቁረይሾች ‹‹አቡ ሱፍያንን›› ለመርዳት ከመካ መንቀሳቀሳቸውን አላወቁም ነበር፡፡ ሆኖም በድር የሚባል ስፍራ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው፤ ሶስት ሶሐቦችን ሁኔታዎችን አጣርተው እንዲመለሱ ወደፊት ላኩ፡፡ የተላኩት ሶሐቦች አጣርተው ሲመለሱም ለጣዖት አምላኪያኑ ውሃ ለመቅዳት የተላኩ ሁለት ሰዎችን አግኝተው በቁጥጥር ስር በማዋል ነበር የተመለሱት፡፡ በእነዚህ ሁለት ምርኮኞች መረጃ መሠረት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ጣዖት አምላኪያን ቁረይሾች ሙስሊሞችን ለመዋጋት ከመካ ወደ መዲና መምጣታቸውን ረሱል صلى الله عليه وسلم እና ሶሀቦቹ ተረዱ፡፡
በዚህን ጊዜ ታላቁ ነብይ صلى الله عليه وسلم በፍልሚያው ዙርያ ሶሐቦቻቸውን አማከሩ፡፡ እንጋፋ ሶሐቦች ተነስተው ውብ ንግግሮችን አደረጉ፡፡
ሙሀጂሮችም አንሳሮችም ሸጋ ሐሳቦችን በማቅረብ አንሸራሸሩ፡፡ ከነዚህ መካከል ‹‹ሰዕድ ኢብኑ ሙዓዝ›› የተባለው ታላቅ ሶሐብይ ይገኝ ነበር፡፡ ሰዕድ የመዲና ነዋሪ ከሆኑት ከአንሳሮች አንዱ ስለነበር፤ አንሳሮች ረሱልን صلى الله عليه وسلم በጭራሽ እንደማይከዱና ባህር ውስጥ እንዲገቡ ረሱል
صلى الله عليه وسلم ቢያዟቸው እንኳ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ገለፀ፡፡ አስከትሎም ረሱልን صلى الله عليه وسلم… ‹‹በአላህ ረድኤት እኛን ይዘህ (ወደ ፍልሚያው)
ጉዞህን ጀምር››… የሚል ከፍተኛ የድጋፍ ሐሳብ በማቅረብ ታዛዥነታቸውን አረጋገጠ፡፡
ከዚያም ረሱል صلى الله عليه وسلم እንዲህ በማለት ሠራዊቱን አስከትለው ጉዟቸውን ጀመሩ፡…… ‹‹አይዟችሁ፤ አላህ ከሁለቱ ጭፍራዎች መካከል አንዱን
(እንደምናገኝ) ቃል ገብቶልኛል››……. ማለትም ወይ የነጋዴዎችን ጭፍራ አግኝተን ንብረቱን መማረክ አሊያም ለነጋዴዎቹ ከለላ ለመስጠት ከመካ ተንቀሳቅሶ የመጣውን የጣዖት አምላኪያኑን ሰራዊት በመግጠም ድል ማድረግን፤ …..ለማለት ነው፡፡ ከዚያም ተጓዙና በድር ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ አቅራቢያ ውሃ የተጠራቀመበት ጉድጓድ ባለበት ቦታ ላይ ረሱል صلى الله عليه وسلم እና ሶሐቦቹ ሰፈሩ፡፡
ሆኖም ግን ጣዖት አምላኪያኑ ከለላ ሊሰጡት ከመካ ተነስተው የመጡለት፤ ‹‹አቡ-ሱፍያን›› የሚመራው የነጋዴዎች ጭፍራ መትረፉና ወደ መካ መድረሱ፤ ለጣዖት አምላኪያኑ ሠራዊት ዜናው ደርሷቸው ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ወደ መካ መመለስን አሻፈረኝ በማለት….. ‹‹ነብዩን صلى الله عليه وسلم ሳንዋጋ አንመለስም››….. ብለው ሙጭጭ አሉ፡፡ ይህም ለነብዩ صلى الله عليه وسلمስር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ ስለነበራቸው ሲሆን እንዲሁም
ረሱል صلى الله عليه وسلم ለሚያደርጉት የዳዕዋ ጥሪ እና ለተከበሩት ሶሐቦቻቸው ከነበራቸው ምቀኝነት የተነሳ ነበር፡፡
ከዚያም አላህ /ሱ.ወ/ ቀለል ያለ ካፊያ ዝናብን አዘነበ፡፡ በረሱል صلى الله عليه وسلم እና በሶሐቦቻቸው እግር ስር ያለው አፈር እርሰ በእርሱ ተያይዞ
ለመራመድ ምቹ ሆነ፡፡ ጣዖታውያኑ ግን ከስራቸው ያለው አሸዋ እግራቸውን እና የግመሎቻቸውን እግር እያሰመጠ በመቀርቀር መሰናክል ሆኖ አዘገያቸው፡፡
ሙስሊሞቹ በድር በሚባል አካባቢ ትልቅ የጉድጓድ ውሃን አቅፎ የያዘውን ኮረብታማ ቦታን ከበቡ፡፡ ከዚያም ጣዖታውያኑ ከዚህ ውሃ ለመጠጣት በመጡ ጊዜ፤ ሙስሊሞቹ አንድ፣ ሁለት፣… እያሉ እነሱን እያለሙ ማደን ጀመሩ፡፡ ሁለቱ ሰራዊቶችም ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡ ከሙስሊሞቹ ሰራዊት ውስጥ ‹‹ላኢላሃ ኢለላህ››ን ከፍ ማድረግ የሚፈልጉ ታላላቅ ሶሐቦች ነበሩበት፡፡ የካሃዲያኑ ሰራዊት ደግሞ ምርጡን ነብያችንን صلى الله عليه وسلم ለመግደል እና ዳዕዋቸውንም እስከወዲያኛው ለማንኮታኮት የተዘጋጀ ነበር፡፡
ሙስሊሞቹ 2 ፈረሶችና 70 ግመሎች ብቻ የነበራቸው ሲሆን፤ ጉዞውን እንኳ ሲገፉ የነበረው በየግመሉ ላይ 3 ሰዎች እየተፈራረቁና እየተተካኩ ነበር፡፡ ሙሽሪኮቹ ግን አንድ መቶ ፈረስ፤ ስድስት መቶ ከብረት የተሰራ የጦር መከላከያ ልብስ እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ አጅግ በጣም ብዛት ያላቸውን ግመሎችን ይዘውና ታጥቀው ነበር፡፡ አያችሁ ከፍተኛ የሆነ የቁጥርና የትጥቅ አለመመጣጠን በሙስሊሞቹ እና በሙሽሪኮቹ መካከል በግልፅ ይስተዋላል፡፡ ሱብሐነላህ!
የሙስሊሞቹ የውጊያ ስልት ረሱል صلى الله عليه وسلم በነገሯቸው መልኩ ነበር የሆነው፡፡ እሱም፡… ጣዖት አምላኪያኑ መጥተው እስከሚከቧቸው ድረስ
ፍልሚያውን እንዳይጀምሩ ነበር፡፡ ጣዖት አምላኪያኑ ከበዋቸው ሲጀምሩ ግን፤ መጀመሪያ ከኮረብታው ጀርባ ዙርያውን ከበው የተሸሸጉት
ሙስሊም ጦር ወርዋሪዎች ብቅ ይሉና የካሃዲያኖችን ጀርባ በጦራቸው እሩምታ እንዲደበድቡ ነበር፡፡ እንደታሰበውም በዚሁ መሰረት ተካሄደ፡፡
በዚህ በረመዳን 17 ዕለት፤ እጅግ ከባድ ውጊያ ተደረገ፤…. ጎራዴዎች ተጋጩ፤…. ጦሮች የእሳት ብልጭታን ፈጠሩ፤…. አቧራ ቦነነ፤… ተክቢራዎች በከፍተኛ ድምፅ ተስተጋቡ፤… ደሞች ፈሰሱ፤… አካላት ተቆራረጡ፤….. አጥንቶች ተከሰከሱ፤….. ግዙፍ የሆነ የአላህ ድጋፍም በዚህ በ‹‹የውመል ፉርቃን›› ተከሰተ፡፡
በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ በተከፈተበት ዕለት አላህ /ሱ.ወ/ የነብዩን صلى الله عليه وسلم ሰራዊት በሺዎች በሚቆጠሩ መላኢኮች አጠናከረው፡፡ መላኢኮች
በፈረሶቻቸው ሊዋጉ መጡ፡፡ ጅበሪል /ዐ.ሰ/ እየመራቸው ሙስሊሞችን ወግነው መዋጋት ጀመሩ፡፡ የሙሽሪኩን ሰራዊት ለማጥፋት አንድ መላኢካ በቂ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሺዎች የሚቆጠሩ መላኢኮች መምጣታቸው የሙስሊሞቹን ክብርና ማዕረግ ለማሳየት አላህ /ሱ.ወ/ ያደረገው ታላቅ ክስተት ነበር፡፡
በዚህ መላኢኮች በተሳተፉበት ጦርነት ማነኛውም ሶሐባ በያዘው ሰይፍ ወደ አንድ ጣዖት አምላኪ ወታደር ገና ሲጠቁም፤ ሰይፉ አንገቱጋ ከመድረሱ በፊት የጣዖት አምላኪው አንገት ተቀንጥሶ ይወድቅ ነበር፡፡ ይህ መላኢኮች በአላህ ትእዛዝ የፈፀሙት ተግባር ነበር፡፡ በዚህም የሙሽሪኮቹ ሽንፈት ሆነ፡፡ ከሙስሊሞች አስራ አራት ሶሐቦች ብቻ የተገደሉ ሲሆን፤ ከሙሽሪኮች ግን በርካቶች ተገደሉ፤ በርካቶችም ተማረኩ፡፡ ከተገደሉት አጋሪያን መካከል የክህደት ቁንጮ የነበረው፤ ‹‹አቡ ጀህል›› እና ሀበሸውን ቢላልን /ረ.ዐ/ ሲያሰቃይ የነበረው ‹‹ኡመያ ኢብን ኸለፍ›› ይገኙበት ነበር፡፡
በስተመጨረሻም ነብዩ صلى الله عليه وسلم እና ምርጥ ሶሀቦቻቸው ድል አድርገውና ተከብረው ተመለሱ፡፡ በዚህ በትጥቅም ሆነ በብዛት ሙስሊሞቹ አጅግ
አናሳ በነበሩበት በበድር ጦርነት፤ 313 ሙስሊሞች በዚያ ሰውነትን በሚለበልበው በረሃ፤ ፆመኞች ሆነው፤ በሶስት እጥፍ የሚበልጧቸውን እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ 1 ሺህ የሚጠጉ ከሀዲያንን ተፋልመው አሸነፉ፡፡ ይህ እንግዲህ ድል ለማድረግ ወሳኙ ቁሳቁስና ብዛት ሳይሆን ጠንካራ ኢማን መሆኑን አመላካች ሲሆን በተጨማሪም ጥቂቶች በኢማናቸው ጠንካሮች ከሆኑ ብዙኃንን ማሸነፍ እንደሚችሉ የሚያስረዳ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ይህ ረመዳንን መፆም አላህ ግዴታ ካደረገ በኋላ፤ ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ የፆሙት የረመዳን ወር፤ የመጀመሪያውን ታላቅ የኢስላም ድልን አስተናገደ፡፡ ታላቅነቱን ለማሳየት አላህ በቁርአኑ ውስጥ… ‹‹የውመል ፉርቃን››… እወነትና ሐሰት የተለየበት ዕለት፤ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ይህ የበድር ዘመቻ ቀን ተጨቁነው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሙስሊሞች የበላይነትን የተቀዳጁበት፣….. ከሀዲያኖች ደግሞ የተንኮታኮቱበት፤….. እውነትና ሐሰት የተለየበት፤….. የኢስላም ጮራ ደምቆ የፈነጠቀበት፤…. ታላቅ ቀን ነበር፡፡ በዚህ በበድር ዘመቻ ቀን ደምና አጥንት ተከፍሎ በተገኘው አንፀባራቂ ድል ምክንያት ኢስላም ነፃነቱን አውጆ ወደየአለማቱ መስፋፋቱን በመቀጠል እኛምጋ ደረሰ፡፡ በእርግጥም ‹‹የውመል ፉርቃን›› ነበር፡፡ ታሪክ በብርሃን ፊደላት መዝግቦታል፡፡
ረመዷን 17 ወሳኝ ዕለት ፈፅሞ ከኡመቱ ቀልብ አትጠፋም ። አላህ መልካም ኢባዳዎቻችንን ይቀበለን ይህ አስከፊ በሽታም አላህ በራህመቱ ያጥፋልን።