በሙቀት ከመከራከር በእውቀት መመካከር!

በሙቀት ከመከራከር በእውቀት መመካከር!
ሰሞኑ በሀገራችን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የምርጫ ጊዜ ማራዘም በሚመለከት በፖለቲካ እና በህገ አንፃር እየተበጠረና እየተነጠር ቅቤ አልወጣው እንደለ ወተት ሆኖ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከሮና ተወጥሮ ክርክር እየተጧጠፈ ይገኛል፣ የሚቀጥልም ይመስላል።
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ምርጫ ጊዜ የሚራዘምበት ህገ መንግስታዊ ምክንያትም መነሻም የሚገልፅ ድንጋጌ የለውም። የምርጫ ጊዜን ለማራዘም ስልጣን የተሰጠው መንግስታዊ አካልም በጭራሽ የለም።
የፌድራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ጊዜ ማራዘም ወይም እንዲተላለፍ የመወሰን ህገ መንግስታዊም ሆነ ህጋዊ ስልጣን የለውም።
የፌድራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ ላይ በተሰጠው ስልጣን አንዳችም የምርጫ ጊዜ ማራዘም የሚችልበት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጠቀሰ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌም በጭራሽ የለም።
የፌድራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ መንግስቱ ባልተሰጠው ስልጣን መወሰን መሰረታዊ ህገ መንግስትን ድንጋጌ በግላጭ መጣስና መደርመስ ውጤት የሚያሰከትል እንደሚሆን ነው።
መሰል ውሳኔዎች የመወሰን ስልጣን መመዘኛና ህጋዊነት የሚለካው በህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች መሰረት ሲሆን ይህም በህገ መንግስቱ ”የህገ መንግስቱ የበላይነት” በሚደነግገው አንቀፅ 9 መሰረት ነው።
የፌድራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ በህግ ሲመዘን የህገ መንግስቱ አንቀፅ 9(1) መሰረት ”ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፣ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡”
የሚለውን ድንጋጌ የሚፃረር ተግባር ነው። ስለዚህም የምርጫ ጊዜ ማራዘመን መወሰን በሌላ ኃይል ካልሆነ በቀር በህግ መቆም የማይችል፣ በህግ ከተሰጠ ስልጣን ውጪ የተወሰነ(ultravirus decision)፣ ህጋዊ መሰረት የሌለውና ሊፈፀም የማይችል ውሳኔ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
በዚህ ውሳኔ ማንኛውም የሀገሪቷ ዜጋም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲያከቡሩ የሚያሰገድዳቸው የህግ መሰረት የለም፣ እንዳውም እንዳይፈፀም የመታገልና እምቢተኝነታቸውን የሚያሳዩበት መብት የሚያጎናፅፋቸው ነው።
ውሳኔው ፈራሽና የማይፈፀም ከሆነ ታዲያ መንግስት ምን አይነት አማራጭ ይኖረዋል የሚለውን በተጎዳኝ ማየት ተገቢ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ መንግስት አራት አማራጮችን፣ አስቸኳይ ጊዜ ማወጅ፣ ፓርላማን መበተን፣ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ጥያቄ ማቅረብ ወይም ህገ መንግስት ማሻሻል የሚሉትን የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወቃል። እነዚህን ጉዳዮች በህጉ በጣም አጠር ባለመልኩ በሶስት ከፍለን ለማየት እንሞክራለን።
አንደኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ፖርላማን መበተን የሚሉ አማራጮች አሁን በስራ ላይ ያለው ተወካዮች ምክር ቤት ቀሪ የስራ ዘመኑና ማጠናቀቂያ የስራ ዘመኑ መቃረብ፣ በእነዚህም መሰረት ከተወሰነም ከጊዜው አንፃር አዋጪነት የላቸውም፣ እነዚህን ለመወሰን የሚያስፈልጉ ጠንካራ ምክንያቶች ያለመኖር ፣ የምክር ቤቱና አስፈፃሚው መንግስት ከነሃሴ በኃላ ህጋዊ(legitimacy) ማጣት በመሳሰሉት ምክንያቶች ምርጫን ለማራዘም የመንግስት ስልጣን ህጋዊነት ለማረጋገጥ ሁለቱም አዋጪ ስላልሆኑ የሚመረጡ አይደሉም።
ሁለተኛ፣ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እንዲስጠበት ለሚመለከተው አካል መተላለፍ እንዲታይ በፖለቲካ ሳይሆን strictly በህገ መንግስታዊ ይዘትና ማዕቀፍ ከታየ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል ከመጠቆም ያለፈ አማራጭ ተርጎሚው አካል እንደማያቀርብ የህገ መንግስቱን እያንዳንዱን አንቀፅ በጥንቃቂ የተመለከተና የፈተሸ ሰው መረዳት ይቻላል። ስለዚህም ህገ መንግስት ተርጎሚው ፌድሬሽን ምክር ቤት ወደ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሃሳብ እንዲፈፀም ሊመራ ይችላል።
ሶስተኛ፣ በህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ የምርጫ ማራዘም ጉዳይ ከታየ ብቸኛ ህጋዊ አማራጩ ህገ መንግስቱን ማሻሻል ብቻ ነው። በፌድሬሽን ምክር ቤት ቢታይም ባይታይም የምርጫ ማራዘሚያ ድንጋጌ የህገ መንግስት ማሻሻያ በማንኛውም ዘመን መደረግና የሚያስፈልግ ነው። ህገ መንግስቱ ቁልፍ የዘነገው ጉዳይ ነው። በአብዛኛው ሀገራት ህገ መንግስት የሚገኙ ጉዳይ ነው። በዚሁ በሀገራችን በአብዛኛው ክልሎች ህገ መንግስታት የሚገኝ ነው። ምርጫ 97 ጊዜ በምርጫ ውጤት ውዝግብን ተከትሎ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ህጋዊነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ በመሆኑ በማንኛውም መልኩ ምርጫው ቢራዘም ወይም የምርጫ ውጤቱ ከተራዘሙ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት/ፓርቲ ህጋዊ የማስተዳደር ስልጣን እንዲኖረው የሚያስችል ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ አብዛኛው ክልሎች ያደረጉ ሲሆን የፌድራሉ ግን ህገ መንግስቱ የማሻሻል ሃሳብ በወቅቱ ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች በተለየም የአንቀፅ 39 ውዝግብና ጭቅጭቅ ያስነሳል በሚል ፍራቻ አልተገፋበትም።
አሁንም ቢሆን ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ የፖለቲካ ጫጫታ ማስነሳትና አወዛጋቢነቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም ህጋዊነቱና ተፈፃሚነቱ ግን ከማንኛውም በላይ ነው። ሆኖም ግን አሁን ከቀረው አጭር ጊዜ አንፃር ህገ መንግስቱን ሙሉ በሙሉ የማሻሻል ይዘት ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ የምርጫ ማራዘሚያ የሚመለከት ክፍል ብቻ ማሻሻል ይገባል። የምርጫ ማራዘሚያ ጊዜ የሚሻሻለው በሶስት መሰራታዊ ጭብጦች ያጠነጠነ ይሆናል።
ይህም ምርጫ ጊዜ የሚራዘምባቸው ምክንያቶች መዘርዘር፣ መራዘምን የሚወስንና የሚያፀድቅ አካል መወሰን እና የምርጫ ጊዜ በሚራዘምበት ወቅት በስልጣን ላይ ያለው ምክር ቤትና መንግስት ስልጣን የሚቀጥልበት ህጋዊነትና የስልጣን ገደቡን(limitation and scope) የሚገልፅ ድንጋጌዎች በህገ መንግስቱ ማሻሻያነት ሊካተቱ ይገባል።
በቀጣይ በህገ መንግስቱ ስርዓት ህገ መንግስቱ እንዴት ይሻሻላል የሚለውን የህገ መንግስቱን ድንጋጌዎች እናያለን።
አንቀጽ 104 የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብን እንዴት እንደሚመነጭ ይደነግጋል። የዚህ አንቀፅ ድንጋጌ ይዘት እንደሚከተለው በህገ መንግስቱ ተቀምጧል።
አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው፣ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የደገፉት ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል፡፡
በዚህ ድንጋጌ መሰረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ለማመንጨት በተወካይች ምክር 2/3 ድምፅ ወይም ፌድሬሽን ምክር ቤት 2/3 ድምፅ ወይም 3 ክልሎች በድምፅ ብልጫ እንዲደግፉት በማድረግ ማሻሻያ ሃሳብ ማቅረብ በጣም ቀላል ስራ ነው። ሆኖም ግን ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብ ማቅረብ የሚለው ግን በህገ መንግስት በምን መልኩና ስርዓት እንደሚፈፀም የተገለፀ ነገር የለም። ከዚህ ቀደም ህገ መንግስቱ ሁለት ጊዜ ሲሻሻል ለህዝብ ወይይትና ውሳኔም የቀረበበት ሁኔታ አልነበረም። ለሀገር ደግና ጥሩ ነገር ማመንጫትና የማወያየትና የመወሰን ተሳትፎ ለማንም ዕድል መስጠት የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም፣ ለዚህም ለህዝብ ውይይትና ውሳኔ ማቅረብም የባለቤትነትና የተፈፃሚነት ብቃት የሚያጎለብት ስለሆነ የሚከፋ አይደለም።
በአለም ላይ ያሉ ሀገራት የህገ መንግስት ማሻሻል ታሪክ መላ ህዝቡን አሳትፎ የተወሰነበት ታሪክ አልተመዘገበም። በስዊዘርላንድ በህዝበ ውሳኔ የሚፀድቅበት ስርዓት የመከተል ታሪክ የኖራቸው ቢሆን ከባድ ፈተና ገጥሟቹው የማሻሻያ ሂደቱን ያላዘቡበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበር። በኢትዮጵያ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብ በማቅረብ ለመፈፀም ዝርዝር ህግና ስርዓት ስለሚያስፈልገው አሁን በቀሪው አጭር ጊዜ የሚታሰብ አይደለም። ወሳኙ ግን የማፅደቅ ስርዓትና ስልጣኑ እንዴት እንደሚፈፀም ላይ ማትኮር ነው።
በህገ መንግስቱ የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች በሁለት አይነት ማለትም ላላ (flexible) እና ጠበቅ ባለ(rigid) መልኩ የሚሻሻሉ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል።
አንደኛ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚመለከቱ ድንጋጌዎች እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብን ስለማመንጨት የሚደነግገው አንቀፆች የሚሻሻሉት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 105(1) ጠበቅ ባለ ስርዓት መሰረት፦
”ሀ/ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት፣
ለ/ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና
ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው”፣ በማለት የሚጠይቅ ስርዓት ነው
ሁለተኛ ”ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኊን ብቻ ይሆናል፤
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት፣ እና
ለ/ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎቸ ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው” ይላል
በነዚህ ድንጋጌዎች የምርጫ ጊዜ ማራዘሚያና የሚያስከትለው ውጤት ድንጋጌ ሊሻሻል የሚችለው በሁለተኛው በተቀመጠው ቀለል ባለ የማሻሻያ ስርዓት ይሆናል።
የፌድራል ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና በፌድራል ደረጃ ተወካዮቹ ከልሆኑ በስተቀር ሁሉም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የብልፅግና ፓርቲ አባላቶች ወይም አካላቶች በመሆናቸው የፌድራል ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ በ2/3 ድምፅ የማፅደቅ እና ከ9 ክልል ምክር ቤቶች 6 ክልሎች የሚያስፈልግ ቢሆንም 8 ክልሎችም በብልፅግና ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ በመሆኑ በአብላጫ ድምፅ በማፅደቅ ህገ መንግስት የመሻሻል ውሳኔ ለመድረስ ከአንድ ሳምንት በላይ ጊዜ በፌድራል መንግስት የሚወስድበት አይደለም።
ስለዚህም ህጋዊ መስመርና ማዕቀፉን በመጠበቅ ሳይወሳሰብ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ሀገሪቷን በቀጣይ ሊገጥማት ከሚችል ከህጋዊ ስልጣን ቀውስ፣ መንግስት አልባነት፣ ክፍተትና ከሚያስከትለውን አደጋ በቀላሉና በህጋዊ መልኩ መቀልበስ የሚቻል እንደሚሆን ነው።
ይህ ከልተደረገ ግን ከነሃሴ ወር መጨረሻ በኃላ የትኛውም አይነት ውሳኔ በመንግስት ቢተላለፍ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህጋዊነትና ቅቡልነት የሚያረጋግጥ አይሆንም።
በዚህም ህገ መንግስቱ ቀጣይነት (contiunity) የሚያሳጣ ወይም suspend የሚያደርግ ወይም abrogate የሚያደርግ እና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ገዢው ፓርቲና የተለያዩ አካለት የሚሳተፉበትና ስልጣን የሚጋሩበት፣ ከፍተኛ ድርድርና ስምምነት የሚያስፈልገው የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጥያቄ የሚቀርብበት የውዝግብና የብጥብጥ ስርዓት እንዲፈጠር በሰፊው የሚጋብዝ እንደሚሆን ይገመታል።