በአዲሱ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ፖርቲዎች ውህደት በሚመለከት ምን ይላል?
~~~
ሰሞኑን በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ህልውናቸውም በማክሰም በውህደት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር የተዋህዱና ብሎም የተፈራረሙበት ሁኔታን አስተውለናል።
በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፖርቲዎች አዋጅ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚወሃዱበት፣ ግንባር የሚፈጥሩበት እና የሚቀናጁበት ሶስት አይነት የሚጣመሩበት ስርዓት እውቅና ተቀምጦ ይገኛል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባርና መቀናጀት መፍጠር ፓርቲዎቹ በተናጠል ህልውናቸው ሳይከስም በጋራ የሚሰሩበትን አግባብ የሚያመለክት ሲሆን ውህደት ግን የተናጠል ህልውና በማክሰም አዲስ ፓርቲ የሚፈጠርበት ወይም የሚወለድበት የፓርቲ አይነት ነው ማለት ይቻላል።
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የፓርቲዎች ውህደትን በሚመለከት ብቻ በአዲሱ አዋጅ የተወሰነ ምልከታ ለማድረግ ይሞከራል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት በሚመለከት በአዋጁ አንቀፅ 2(25) መሰረት ወህደት ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በህግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጥል ህጋዊ ሰውነታቸውን በመተው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰርቱበት ሂደት ነው ይላል።
ስለፖርቲዎች ውህደት አፈፃፀም በአዋጁ አንቀፅ 92-93 ተመላክቷል። በአዲሱ አዋጅ አንቀፅ 92(1) በአዋጅ መሰረት የተመዘገቡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት እንደሚችሉ ይገልፃል።
በዚህ ደንጋጌ መሰረት …በዚህ አዋጅ የተመዘገቡ….. የሚለው ሀረግ ይዘት የፖለቲካ ፖርቲዎች ከመዋሀዳቸው በፊት በአዲሱ አዋጅ መርህ፣ መስፈርትና መመዘኛዎች መሰረት እያንዳንዱ ፓርቲ ራሱን ከአዋጁ ጋር ማጣጣምና ማስተካከል እንደሚገባው አመላካች ነው።
የአዋጁ አንቀፅ 91(5) በውህደቱ የሚመሰረት የፖለቲካ ፓርቲ እንደሁኔታው የአዋጁ አንቀፅ 64 እና አንቀፅ 65 መስፈርት መሟላት እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህ ደንጋጌ ይዘትና አቀራረፅ እንደሁኔታው የሚለው ፓርቲዎቹ ቀድሞውን በአዋጁ መሰረት በተወሰነ ደረጃ የተጣጣሙት እንደተጠበቀ ሆኖ ባልተጣጣሙት ጉዳዩች እንደ አግባቡ እንዲያስተካኩል አላማን የያዘ ድንጋጌ ነው።
በአዲሱ አዋጅ ከላይ የተጠቀሱት አንቀፆች ድንጋጌዎች በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት አባላት ብዛት 10,000 እና የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት አባላት ብዛት 4000 አነስተኛው(minimum threshold ) የፓርቲ መመስረቻ ቁጥር መስፈርት አንዱ ማሟለት የግድ እንደሚያስፈልግ ነው።
ሌላው ጉዳይ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት ሆነ በክልል ደረጃ ለመመስረት የፓለቲካ ፓርቲ መስራች አባላት በሚያሰባስብበት ጊዜ ፆታን እና የተለያዩ በአከባቢው ያሉ ህብረተስብ ክፍሎችን ተዋፅእ ባገነዘበ መልኩ ራሳቸውን ማስተካከል እንዳለበቸው ነው።
ከዚህ ቀደም በአንድ ብሔር ተደራጅተው ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአስገዳጅ ሁኔታ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በሀገሩ ደረጃ ሁሉንም ብሔሮችና ህዝብች አስተዋፆ እና በክልል ደረጃ ደግሞ በአከባቢው ያሉ ማህበረሰቦችን አስተዎፆ ባገናዘ መልኩ መስተካከል እንዳለባቸው የተቀመጠውን መርህ ጠብቀው መፈፀም እንዳለባቸው ነው።
እስከሁን ድረስ ከሐረሪ ብሔራዊ ሊግ በስተቀር በኢህአዴግም ሆነ በአጋር ድርጅቶች የአከባቢውን የተለያዩ ማህበረሰብ በአባልነት ያቀፈ የለም። እንዲሁም በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች የአከባቢያቸውን ማህበረሰብ አካተው የተደሩጁ ማግኘት የሚከብድ ይሆናል።
አዲሱ አዋጅ በቀድሞ ህግ የተመዘገቡም ፓርቲዎችም ሆነ አዲስ ለሚመሰረቱ ፓርቲዎች የአባቢያቸውን ማህበረሰብ የማቀፍ ግዴታ እንዳለባቸው ነው። በአንድ ብሔር ብቻ የተደራጁ ፓርቲዎች በአዋጁ የተቀመጠውን መርህ የማይከተሉ ከሆኑ የመስረዝ እድል እንደሚገጥማቸው አዋጁ በግልፅ ያስቀምጣል።
አንቀፅ 64 አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት 10000 ከመስራች አባላት ውስጥ 40% የማይበልጡ የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው፣ የተቀሩት መስራች አባላት ነዋሪነታቸው ከኢትዮጵያ ከሚገኙት ሌሎች ክልሎች ውስጥ ቢያንስ በአራት ክልሎች መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው፣ ከየክልሉ ሀገር አቀፍ መስራችነት ከሚመዘገቡት አባላት በእያንዳንዱ ክልል 15% መደበኛ ነዋሪ ሲሆኑ እንደሆነ አዋጁ ይገልፃል።
አዋጁ ከዚህ በላይ የተገለፁት መስራች አባላት እድሜያቸው ከ18ና ከዚያ በላይ ሆኖ በህግ ወይም በፍርድ ቤት ውስኔ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ የፖለቲካ ፓርቲው አባል ለመሆን መስማማታቸውን ከሙሉ ስማቸው ጉን ባኖሩት ፊርማቸው የገለፁና በተመዘገቡበት አከባቢ ነዋሪ ስለመሆናቸው ለፓርቲው ማረጋገጫ ያቀረቡ መሆን እንዳለበቻው ያስቀምጣል።
የመስራች አባላት መረጃ የአባሉ ሙል ስም፣ ፆታ ዕድሜ፣ ቀበሌ ወይም ወረዳ፤ እንደየአግባብነቱ የሚኖሩበት ቦታ ልዩ ስም ወይም የቤት ቁጥር፣ የነዋሪነት መረጋገጫ አይነት፣ ያቀረበው የነዋሪነት ማረጋገጫ መለያ ቁጥር ያለው ከሆነ ሙሉ ቁጥር፤ ፊርማና የመዝገባ ቀን የሚገለፅ እንዲሁም የመረጃ ሰብሳባው ስምና ፊርማ የያዘ መሆን እንዳለበት አዋጁ ይገልፃል።
የአዋጁ አንቀፅ 65 የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት መመዛኛው ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ሀገር አቀፉ የሚገሩት መመዛኛ አብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆንም በመሰረታዊነት የሚለዩት የመስራቾች አባላት ብዛት 4000 መሆን እና አባላቱ 30% የሆኑት የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንደለበቸው ነው።
አዲስ የሚዋሃዱት የፓለቲካ ፓርቲዎች ከመዋሃዳቸው በፊት በአዲሱ አዋጅ የተጠቀሱትን መመዘኛና መስፈርት ከሟሉ በኃላ ለአዲሱ ውሁድ መዘጋጀት እንዳለባቸው የአዋጁ ይዘትና መንፈስ ያስረዳል።
የመዋሃድ ጥያቄ በማንኛውም ጊዜ ሊቀርብ የሚችል ቢሆንም በአዲስ አዋጅ ለመወሃዱ የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄያቸው ጠቅላላ ምርጫና የአከባቢ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ከሁለት ወር በፊት ለቦርዱ ማቅረብ እንዳለበቸው ይገልፃል።
በአሁኑ ጊዜ ለመዋሃድ የሚፈልጉ ፓርቲዎች በአዲስ አዋጅ መሰረት አስፈላጊውን መስፈርትና መመዘኛ አሟልተው ወደ ውህደቱ እውን ለማድረግ ከምርጫ 2012 የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መቃረበ አንፃር ህጉን ጥሰው ካልፈፀሙ በቀር የሚቻል አይመስልም።
ለመዋሃድ የሚፈልጉ ፓርቲዎች አቀራረብን በሚመለከት በአዋጁ አንቀፅ 91(3) ለመዋሃድ የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውህደቱ የሚቀረቡ ማመልከቻዎች መካተት ያለባቸው ዝርዝር ጉዳዩች ያስቀምጣል።
እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ፓርቲው ውህደቱን የተቀበሉ ስለመሆኑ የሚገለልፅ ውሳኔ፤ ፓርቲዎች ስለውህደቱ ዝርዝር ጉዳዩች ያደረጉት የጽህፍ ስምምነት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲዋሃዱ የሚኖረው አዲስ ስምና በአዋጁ አንቀፅ 67 የተዘረዘሩት ሰነዶች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ደንጋጌ ይዘት የፖለቲካ ፓርቲዎች በህገ ደንቡ መሰረት የውህደቱ ስምምነት ውሳኔ በየጠቅላላ ጉባኤ አስወስነው የተፈራረሙበት፣ ስለውህደቱ ዝርዝር ጉዳዩች የሚመለከት እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጽህፍ ስምምነት ያደረጉበት ሰነድ እና አንድ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ሰነዶችን በተሟላ መልኩ ማቅረብን ይጠይቃል።
የወንጀል ክስ የቀረበት ፓርቲን በሚመለከት በአዋጁ አንቀፅ 91(6) ውህደቱ ለመፈፀም የሚፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ ለመሰረዝ ውይም ለማፍረስ ሊያደርስ በሚችል ወንጀል ክስ የቀረበበት እንደሆነ ፓርቲው የክሱ ውሳኔ ሳያገኝ ወይም ሳይዘጋ መዋሃድ እንደማይችል ነው።
ለውህደቱ አስፈላጊው መስፈርት ሲሟላ በአዋጁ አንቀፅ 91(4) ቦርዱ የቀረበለት የውህደቱ ጥያቄ በህጉ መሰረት ቀርቧል ብሎ ሲያምን ለተዋሃዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰጥቶ የነበረው የምስክር ወረቀት ይሰርዘዋል፣ አዲሱን ፓርቲ በአዋጁ መሰረት በአንድ ወር ውስጥ ይመዘግባል። ቦርዱ የእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ንብረት፣ ገንዘብና አስፈላጊ ሰነዶች በውህደት ወደ ተመሰረተው የፖለቲካ ፓርቲ በስድስት ወር ጊዜ እንዲተላለፍ ትዕዛዝ ይሰጣል።
አዲስ በውህደት የተፈጠረው ፓርቲ በህግ እውን ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 92 የፖለቲካ ፓርቲ መዋሃድ የሚያስከትለው ውጤት ይገልፃል። ድንጋጌው አዋጁ አንቀፅ 92(1) የአዋጁ አንቀፅ 91(4) እንደተጠበቀ ሆኖ አዲሱ የውህደቱ ውጤት የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ የተዋሃዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወራሽ ይሆናል፣ መብትና ግዴታም ይተላለፍለታል፣ ያለፈው የሂሳብ እንቅስቃሴ ሪፓርት ቦርዱ ሲጠይቅ ያቀርባል፣ የተወሃዱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ፍርድና መብት የሚተላለፍለት ሆኖ የፍተሐብሔርና አስተዳደራዊ ክርክር ተክቶ ያስፈፅማል፣ ይፈፅማል።
በአዋጁ አንቀፅ 92(2) አዲሱ የውህደቱ ውጤት የሆነው የፖለቲካ ፓርቲ በተመዘገበ ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ያስገኘው ሀብት፣ ንብረትና ዕዳ የሚያሳይ የወጪና የገቢ እንቅስቃሴ የሂሳብ ሪፖርት ለቦርዱ ማቅረብ እንዳለበት ያመለክታል።
ቀድሞ ፖርቲ አባል የነበረና አዲስ በተፈጠረው ውህድ ፓርቲ አባል ያለመሆኑ የተጠበቀ ነው። ሆኖም ግን በአዋጁ አንቀፅ 92(3) መሰረት ውህደቱን የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማንኛውም ደረጃ ያሉ የም/ቤቶች ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሰው በውህደቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነ መቀጣል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን እንደሚያጠናቅቅ ይገልፃል።
በውህደት አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት በአዲሱ አዋጅ የተቀመጡት ስርዓቶች ከላይ አጠር ባለ መልኩ የተገለፀው ሲሆን፣ በሀገራችን ወደ ውህደቱ እያመሩ ያሉት ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ በተቀመጡ ህጋዊ ሂደቶችና ስርዓቱን ጠብቆ እስከሆኑ እየተከናወነ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያጭር እና በቀጠይ የሚከናወነቱስ አዋጅ ጠብቆ የማስተካከል ዝግጅት ምን ያህል ነው የሚለው አንገብጋቢ ያድርገዋል።