ለአናሳ ብሔሮች የውህደት ስጋት!~~~~
የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ የኢህአዴግ ድርጅት በመተካት አዲስ የሚቋቋመው ከሀገራዊ ፋይዳው ባሻገር ክልላዊ እንድምታው/implication/ በአግባቡ መታየቱ ተገቢ ይመስላል።
ኢህአዴግ አንድ ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ መፍጠር ማለት ፌደራላዊ ሥርዓቱ ጋር ምንም የሚያጋጨው ነገር ፈፅሞ እንደሌለ ገልጿል ፡፡ እንዲሁም ኢህአዴግ በጣም ግልፅ መሆን ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር ፓርቲን አንድ እናድርግ ሲባል በህገ-መንግስቱና በፌደራላዊ ሥርዓቱ ማዕቀፍ ብቻ እንደሆነም አመላክታል፡፡ ውህደቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት በእኩል የሚወሰንበት፣ ፍትሃዊ እና አካታች የፖለቲካ ውህደት ለመፍጠር መሆኑና በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ማንነትና የጋራ ማንነትን በአግባቡ አስታርቀው ለማስተናገድ እንደሆነምበሰፊው ተዘግቧል። ይልቁኑ ፌደራሊዝም ላይ የሚነሱ ጉድለቶችን በተሻለ ደረጃ በማረም ማስቀጠል የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በዚህ መልኩ የቀረበው የውህደቱ አስፈላጊነት በማያጠራጥር ሁኔታ አሳማኝ ነው። ሆኖም ግን ረቂቅ ህገ ደንቡ አሁን ያለውን የፌድራል ስርዓት በሚያስጠብቅና በሚያጠናክር መልኩ ወደ ወህድ የሚቀለቀሉ ብሔር ድርጅቶች አወካከሉና አሰያየሙ እንዲት ይታያል የሚለው ቁልፍና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው።
ለውህደቱ የተቀመጡ መሰረታዊ ምክንያቶችና ውህደቱን የህግ ማዕቀፍ ለማስያዝ ህገ ደንብ የተቀመጠው አወቃቀርና ይዘት ከሀገራዊ እይታ አንፃር መሰረታዊ ችግር የለውም የሚያስብል ደረጃ ለማስቀመጥ የሚቻል ይሆናል።
ሆኖም በውህዱ ፓርቲ አመሰራረትና የአባላት አመጣጥና አወካከል በመሰረቱ የብሔረሰቦችን የህዝብ ቁጥር ብዛት ግንዛቤ ወስጥ በማስገባት ህገ ደንቡ እንደተረቀቀ ይገልፃል። የአናሳ ብሔሮችን ውክልና ታሳቢ እንደሚያደረግ ይገልፃል። የዚህ አይነት አወቃቀርና አወካከል ቀመረ በህዝብ ብዛትና የአናሳዎች ውክልና ተሳትፎ ታሳቢነት የማድረግ በህገ መንግስቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፌድራል መንግስት የስልጣን ተሳትፎ ታሳቢ ያደረገ አይነት ከመሆኑ አንፃር በሀገራዊ እሳቤ ትክክል ሊሆን ይችላል።
ህገ ደንቡ ሀገራዊ ውህደት እሳቤ ላይ በመሰረታዊነት ትኩረት በማድረጉ በክልል ደረጃና የአናሳዎች (minorities) መብቶችን ከማስጠበቅ አኳያ በግልፅ ውስንነት እንዳለው ያመለክታል።
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀቹ አላማው የመንግስት ስልጣን መያዝ እንደሆነ የሚያወዛግብ ጉዳይ አይደለም። የመንግስት ስልጣን ለመያዝ ፓርቲዎች የሚወዳደሩት በፌድራል ወይም በክልሎች ወይም በሁለቱም ስልጣን እርከን ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል። አዲሱ የውህድ ፓርቲም ህገ ደንብ ምኞት ግን በፌድራል ደረጃ ያለውን ስልጣን ወክልና ታሳቢ በማድረግ የፓርቲ አባላት አወካከል መቃኘትና መወጠኑ የአናሳዎች መብት ከማስጠበቅ እና አሁን ያሉትን በክልሎች አደረጃጀት ወይም ወደ ፊት በክልል ደረጃ ለሚደራጁት ክልሎች ታሳቢ ያላደረገ መሆኑ በግልፅ ያመላክታል።
በፌዴራላዊ ስርዓት እያንዳንዱ ክልል የራሱ ድርጅት ይኑረው የሚል እሴም እንደሌለም ይታወቃል። የፓርቲዎች ህልውና ሳይሆን የማንነት ህልውና ወክልናም በወጉ ሊታይ ይገባል። አንድ ነገር በእርግጠኝነት ለመናገር ግን የመንግስት ስልጣን አወቃቀርና የፓርቲ አደረጃጀት ራሱን የቻለና የተለያዩ ቢሆኑም ፓርቲዎች ግን በህገ መንግስቱ በተቀመጠው የስልጣን ሲስተምና እርከን ታሳቢ በማድረግ ለስልጣን የሚወደደሩ እስከሆነ ድረስ የፓርቲው አደረጃጀት፣ አወካከልና አሰያየም ይህን ታሳቢ መድረግ የግድ ይላል። ስለዚህም የውህድ ፓርቲው አደረጃጀት፣ አውካከልና አሰያየም የፌድራል ስርዓቱን በመከተል በፌድራልና በክልል ደረጃ ያሉትን የስልጣን እርከን እና የአናሳዎች መብትን በሚያስከብር መልኩ ህገ ደንብ በግልፅ በሚቀመጥበት ሁኔታ በታሳቢነት ረቂቁ ሊሻሻል ይገባል።
የሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆኑ ወህደቱ ሀገር አቀፍ ቀመርን ይዞ መሄድ ለሀገር አቀፍ አላማ ተገቢ ብሆንም አሁን ካለው የፌድራል ስርዓት አወቃቀር በክልል ደረጃም አወካከልና አሰያየም በልዩ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በሚረቀቀው ህገ ደንብ ካላመላከተ አንዳንድ ክልሎችና የአናሳዎች የማንነት መብት ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል።
በተለይም የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረሪ፣ የአፋርና በአንዳንድ በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔሮች በአብዛኛው(majoriy) ብሔሮች በመዋጥ ህልውናቸው ሊጠፋ እንደሚችል ያሰጋል።
ስለዚህም የውህድ ፓርቲ የፌድራል ስርዓቱን እንደማያፈርስና እንደማይሽረሽ በተደጋጋሚ እንደተሰጠው መግላጫ በህገ ደንብ አሁን ያለው የፌድራል መንግስትና የክልሎች አወቃቀር፣ የአናሳዎች ውክልና ብቻ ሳይሆን የመንግስትነት ስልጣን ተሳትፎን በሚገባ ካልታየ በወህደቱ አስፈላጊነት አጋር ክልሎች እንደጓጉለትና እንደሰጡት ደጋፍ ላይጠቅማቸው እንደሚችል ይገመታል።