ከዛሬ ጀምሮ ሼኽ አህመድን ጥያቄ ጠይቅልኝ ማለት ቀረ!

ከዛሬ ጀምሮ ሼኽ አህመድን ጥያቄ ጠይቅልኝ ማለት ቀረ!

“ኢና ሊላሂ ወኢና ኢሌይሂ ራጂኡን “
ታላቁ አሊም ሼኽ አህመድ አብዱላሂ በ1922 ዓ/ም በሐረር ከተማ ጀጎል ተወለዱ። ሼኽ አህመድ ተወልደው በሁለት አመታቸው የአይን ብርሃናቸውን አተው ማየት የተሳናቸው እንደሆኑ ይነግራል። ሼኽ አህመድ ማየት የተሳነኝ ነኝ ብለው ሳይቀመጡ ከቁርአን ጌይ እስከ ታላላቅ ሼኾች የዲነል ኢስላም አስተምህሮት መማርን ተያያዙት።
ሁሉም ነገር ለበጎ ነውና ሼኽ አህመድን አላህ ማየት የተሳናቸው ሲያደርጋቸው በምትኩ ልባቸው እና አእምሮዋቸው ከአይኖቻችን በላይ ክፍት በማድረግ ካሳቸው።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ከቅዱስ ቁርአን እስከ በርካታ የሐዲስና የእስልም አስተምህሮት መፅሀፍ በሂፍዝ ያለ ብሬል አጋዥነት የያዙ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሐረር ከሚገኙ አሊሞች የእስልምና እወቀት በመቅሰም በለጋ የወጣትነት እድሜያቸው የእስልምና ሃይማኖት እውቀት ማስተማር ጀመሩ።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ደደር ሃገር ድረስ በመሄድ ለተወሰነ አመት የእስልምና ትምህርት አስተምረዋል።ከዛ በመመለስም በሐረር ከተማ ከስልሳ አመት በላይ ለህዝብ ሙስሊሙ ያለ አንዳች ልዩነት እና ክፍያ ሲያስተምሩ ከርመው በ 90 አመታቸው ግንቦት 23/2012 ከዚች ዱኒያ በሞት ለማንም ወደማይቀረው አኺራ ተጓዙ።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከስልሳ አመት በላይ በአው አብዳል መድረሳና ፣በታላቁ ጃሚእ መስጊድ እና በተጨማሪ ማታም ሳይቀር በቤታቸው በማስተማር ትልቅ አገልግሎት ሰተዋል።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ቀን አው አብዳል መድረሳ ቁርዓንን አስተምረው ከዛም በታላቁ የሐረር ከተማ ጃሚእ መስጊድ ሁሌም ላለፉት ስልሳ አመት በላይ አስተምረዋል።
በጃሚእ መስጊድ ከሚሰጡ የእስልምና አስተምህሮት መካከል የሚከተሉት ናቸው።
ቁርአን ተፍሲር፣ሐዲስ ፣ተውሂድ፣ ፊቅሂ፣ሀያቱ ሳሃባ ፣ሀያቱ ታቢኢን፣ እና ሌሎች የእስልምና ሃይማኖት ትምህርቶችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አስተምረዋል።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰተው ሲያስተምሩ ከማንም ከምንም ጥቅም ፈልገው ሳይሆን የአላህ ወዴታን ለማግኘት እንደሆነ ይናገራሉ።
“ከዚች ከዱኒያ ጥቅማ ጥቅም የአላህ ወዴታ ይበልጣል እኔ ሀያ አራት ሰአት የምለፋው ያን ለማግኘት ነው ይሉ ነበር” አላህ ውዴታውን ይስጣቸው።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ አንድ ቀን ድምፅህን እና ስምህን ከያዙ ከአስር አመት ቡሃላ እራሱ ብትገናኛቸው ገና ድምፅህን ሲሰሙ ስምህን ይጠራሉ ሱብሃነላህ!
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ እጅግ ሲበዛ ተጫዋች፣ከሁሉምጋ ተግባቢ፣ ከህፃናት እስከ አዋቂ የሚወዳቸው እና የሚከበሩ ናቸው። እሳቸው ሲያስተምሩ ሁሉም ነገር እንደ አቅምህ ደረጃ አቅልለው የሚያስረዱ እውቀት የሚያስቀስሙ ልዩ አስተማሪ አሊም ናቸው።
ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ለእስልምና ሃይማኖት በርካታ ሰዎችን በማስተማር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።በሁሉም ዘንድ ደሞ ተወዳጅ ያደረጋቸው የእሳቸው ውብ ሥነምግባር እና ለሙስሊሙ አንድነት ያላቸው አቋም ነው።
ሞት ለማንም አይቀርም ሁላችንም ቀናችንን (ተራችንን)ነው የምንጠብቀው እና ሼኽ አህመድ አብዱላሂም ለአንድ ሳምንት ባደረባቸው ህመም ጆግላ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ግንቦት 23/2012 ሕይወታቸው አለፈች። ሼኽ አህመድ አብዱላሂ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ሰው ስለሆኑ የእሳቸውን ሞት ሁሉንም የሐረር ከተማ እና በመላው አለም ያሉ የእሳቸው ተማሪዎችን አስደንግጧል።
የቀብር ስንስረአታቸው ላይ ከህፃናት እስከ አዋቂ ፣ከከፍተኛ የክልሉ አመራሮች እስከ ታላላቅ እና አንጋፍ የሐረርጌ ኡለማዎች ሼኽ አደም ቱላ ፣ሼኽ ኡስማን ፣ ሼኽ ሙኽታር ፣ ሼኽ ጀማል እና በርካታ አሊሞች በተገኙበት በሐረር አው አብዳል መቀባር ተፈፀመ።
ዛሬ ቀኑ የሸዋል ፆም ተጠናቆ በክልሉ የሸዋል ኢድ የሚከበርበት ቀን ቢሆንም የታላቁ አሊም ሼኽ አህመድ አብዱላሂ ሞት ቀኑን ወደ ሐዘን ቀይሮታል። አዎ ሐረር ታላቅ ሰው ትልቅ የእወቀት ብርሃን ኮከብ አጣች፣ ጨለመች በሐዘንም ተዋጠች።
“ኢና ሊላሂ ወኢና ኢሌይሂ ራጂኡን “
ሼኽ አህመድ ሙሉ ዕድሜያቸውን ለማግኘት ለለፉበት የአላህ ውዴታ አላህ ይስጣቸው። አላህ ይዘንላቸው፣አላህ ጀነቱል ፊርዶውስ ይሸልማቸው። ሌቤተሰቦቻቸው፣ለወዳጅ ዘመዳቸው ፣በመላው አለም ለሚገኙ ተማሪዎቻቸው ሰብርና ኢማን ይስጠን።
አሚን!