አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ የህይወት ታሪክ በአጭሩ

አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ የህይወት ታሪክ በአጭሩ

በ1947 በድሬደዋ ከተማ በአሁኑ ጫት ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተወለዱ:: አቶ አብድይሰመድ ኢድሪስ በመጀመሪያ ወደ ትምህርት ሲቀላቀሉ መካሪ መላህላ በሚል የሀይማኖት ት/ቤት የአረብኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::  

የመደበኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በለገሀሬ ት/ቤት በ3 አመት ውስጥ በሴሚስተር እያለፉ 7ተኛ ክፍል ደርሰዋል::  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ለ1 ዓመት ያህል ከተከታተሉ:: በኋላ በወቅቱ በነበረው እድገት በህብረት ዘመቻ በኦጋዴን ይዘምቱና በዘመቻው ትንሽ እንደቆዩ /ዘመቻውን ሳይጨርሱ/ ኤች.ፒ.(HP) የሚባል የስኳር ፋብሪካ ውስጥ በኢንስፔክተርነት ሰርተዋል፡፡

በ1960ዎቹ አመሸና የሚባል ት/ቤት ከሌሎች ጓኞቻቸው ጋር በመሆን ለማቋቋም ቻሉ፡፡ የዚህ ት/ቤት አላማም በወቅቱ የሀረሪ ሴቶች የሀይማኖት ትምህርት፣ የእጅ ስራን እና የቤት አስተዳደርን ከተካኑ ከዚያ በኋላ መደበኛ ትምህርትን እንዲቀላቀሉ ማስቻል ነበር::  ትምህርቱ በሀረሪኛ ቢሰጥም ማንኛውንም ብሔረሰብ ይማርበት  ነበር፡፡ አቶ አብዱሰመድ ት/ቤቱን ከማቋቋም ባለፈ የትምህርት ቤቱ ዳሬክተር በመሆንም ሰርተዋል:: በልጅነት እና በተማሪነት ዘመናቸው ስፖርትን ይወዱ እንደ ነበርና በመረብ ኳስ እና ብስክሌት ውድድሮች ይወዳደሩ እንደ ነበርም ያስታውሳሉ፡፡  በወቅቱም ቀይ ሽብር ይፋፍሞበት የነበረ ጊዜ ስለነበር እሳቸውም የእስሩ ተቋዳሽና በስም ስህተት ምክንያት ከሞት ሊተርፉ እንደ ቻሉም ገልፀዋል:: ይኸውም አቶ አብዱልሰመድ ኢድሪስ በማለት ፋንታ አብዱል ሰሚድ እንዲሪስ በማለት “እንደ ተፈለኩ ሲጠሩኝ ስሜ አይደለም በማለት ህይወቴን ለማትረፍ ችያለሁ፡፡” ይላሉ::

 በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ወደ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ በአ.አ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ተቀብለው በወቅቱ ከፋ በመባል ይታወቅ በነበረው ክፍለ አገር የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነው አገለገሉ:: ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ድሬደዋ በመመለስም በ1975 ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ ከህንዱ ቻይልድ ወልፊር ዩኒቨርሲቲው ተቀብለዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ጎን ለጎን ዱኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት ውስጥም ይሰሩ እንደነበር ይናገራሉ:: የተለያዩ የስጋ ደዌ ህሙማንን በእርሻ ለማቋቋም በድሬደዋ ገንደ ተስፋ በአሰበ ተፈሪ ገንደ ድኩማን በሀረር ገንደፌሮ በተለይ በድሬደዋ ያሉ ህሙማኖችን እስከ ጅቡቲ ድረስ ተግባራቸውን ቀጠሉበት:: ከዚህ በመቀጠልም የአይነ ስውራን ማህበርን በማቋቋም በተለያየ የስራ ዘርፍ የስጋጃ ስራ እና በሳሙና ስራ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል:: ከዚህ በጎ ስራ ሳይወጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ፕሮጀክት በማቋቋም ወደ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ጎዳና ተዳዳሪዎችን በማደራጀት ህይወታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚለውጡበትን ሁኔታ በመንደፍ ከፍተኛ የበጎ አድራጎት ስራ ሰርተዋል፡፡ ከዚያም በ1986 ዓ.ም ወደ ሀረር በሹመት በፀሐፊነት መጥተዋል:: በዚህ የክልሉ ጸሐፊነታቸው ክልሉን የማደራጀት፣ የማቆም በጀትን ስራ ላይ የማዋል ሀላፊነትን ወስደው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ የኋላ ኋላ ግን አይናቸው እየተዳከመ በመምጣቱ ለብዙ ስራዎች እንቅፋት መሆኑ አልቀረም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ተለያየ የውጪ አገራት ሄደው ለመታከም በቅተዋል፡፡

የሀረሪ ክልልን ለማቋቋም ጄኔራል አሊ አብዲ አቡበከር እና እሳቸው ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ ጀኔራል አሊ፣በአስተዳዳሪነት አቶ አብዲ አቡበከር በም/አስተዳዳሪነት እና እሳቸው በዋና ጸሐፊነት ሆነው አገልግለዋል:: በአዲስ መልክ ከመደራጀቱ በፊት በምስራቅ ኦሮሚያ ትተዳደር የነበረችውን የሀረሪ ክልል በማዋቀር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው አለመግባባትና በሀሳብ ልዩነቶች አቶአብዱልሰመድም በ3 ጥይቶች ተመተዋል:: ነገር ግን አስፈላጊውን ህክምና ስለ ተደረገላቸው ህይወታቸው ሊተርፍችሏል፡፡

አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ ሀገራቸውን በተለያዩ የሀላፊነት መስኮች ያገለገሉ ሲሆን ለአብነትም በደርግ ዘመነ መንግስት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የድሬደዋ ቅርንጫፍ ሀላፊ በመሆን ሰርተዋል፡፡በሽግግር መንግስት ወቅት በሀረሪ ክልል ምስረታ ላይ ዋና ተሳትፎ የነበራቸውና አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ 

የሀረሪ ክልል በመጀመሪያ እንደ ክልል 13 ሲመሰረት የፌደራሉ መንግስት በክልሉ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲ ሰጡ ከመደባቸው ሶስት አመራሮች መሀል አቶ አብዱሰመድ አንዱ ነበሩ፡፡

እንዲሁም የሀረሪ ብሄራዊ ሊግን ከመሰረቱ የቀድሞ አመራሮች ውስጥም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አቶ አብዱሰመድ የክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ፡ የባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ አማካሪና በሀረሪ ህዝብና ምስራቅ ኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳዮች የመረጃ ምንጭነት አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አማካሪም ነበሩ፡፡

በተለያዪ አለም አቀፍ ተቋማትም በአማካሪነት የሰሩት አቶአብዱሰመድ የአለም ሰላም ማህበር (world peace association) አማካሪ እና የማህበሩ አመራር በመሆን አገልግለዋል፡፡  አቶ አብዱልሰመድ እንድሪስ የሀረሪ ብሔራዊ ሊግን ካቋቋሙት የሀረር ባለውለታዎች አንዱ ናቸው፡፡

ከሚያስደስታቸውም ነገሮች እውነት መናገር ዋነኛው እንደሆነ ሲጠቅሱ ውሸቶች ያስጨንቁኛል፣ መናገርም አልፈልግም፣ይላሉ፡፡ ሌላው ከሚያስደስተኝ ማንበብና ማዳመጥ አሁን ላይ ግን ሬዲዮ በተለየ ለኔ ጓደኛ ነው ካለ ሬዲዮ መኖር አልችልም፣ሬዲዮ አጠገቤ ካለ ብቸኝነት አይሰማኝም ሲሉ ለሬድዮያላቸውን ፍቅር ይገልፃሉ፡፡

በሀረሪ የህዝብ ታሪክ ላይም ብዙ ምርምሮችን አድርገው ለብዙ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የማመሳከሪያ ቃላቸውን ሲሰጡ ኖረዋል፡፡  

አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ ባደረባቸው የኩላሊት ህመም ምክንያት ቱረክ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ የነበረ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ህክምናቸውን ሲያደርጉ በነበሩበት ሆስፒታል  ማረፋቸውን ቤተሰባቸው አስታውቋል።

በቱርክ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ባደረባቸው ህመም ግንቦት 5 ቀን 2013 አመት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በአቶአብዱሰመድ ኢድሪስ ህልፈት የተሰማንን ሀዘን እየገለፅንለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡

To view the Video click here.